Monday, February 17, 2014

መቼም ዛሬ ወደ ሮም ሲሄድ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መጠለፉንና በሮም ፈንታ ጄኔቭ ላይ ለማረፍ መብቃቱን ሁላችንም ሰምተናል፡፡



መቼም ዛሬ ወደ ሮም ሲሄድ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መጠለፉንና በሮም ፈንታ ጄኔቭ ላይ ለማረፍ መብቃቱን ሁላችንም ሰምተናል፡፡

ነገሩ ማንምና ምንም ሳይጎዳ በቁጥጥር ስር መዋሉ ቢያስደስተንም ሁኔታው ግን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

እስካሁን ባለው የሚታመን ዜና መሰረት ጠላፊው የአውሮፕላኑ ረዳት አብራሪ ነው፡፡ ረዳቱ አብራሪ ራሱ የሚያበረውን አውሮፕላን ለምን ጠለፈ? ‹‹ሀገሬ ስላልተመቸችኝ የስዊዘርላንድ መንግስት ጥገኝነት እንዲሰጠኝ ለመጠየቅ›› ብሏል አሉ፡፡ ...

‹‹አሉ››ን አትርሱ እንግዲህ!

ጠላፊው ረዳት አብራሪው መሆኑን የዜና ምንጮች እየተቀባበሉ ከማወጃቸው በፊት ደግሞ አቶ ሬድዋን ሁሴን ‹‹ጠላፊው ወይም ጠላፊዎቹ አውሮፕላኑ በፕሮግራሙ መሰረት ካርቱም ላይ ባረፈ ጊዜ የተሳፈሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ›› መግለጫ ቢጤ ሰጥተው ነበር፡፡

እንግዲህ አሁን በሰማነው ዜና መሰረት ደግሞ አውሮፕላኑ በጭራሽ ሱዳን አላረፈም፡፡ ታዲየ አቶ ሬድዋን ዋሹ እንዳይባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት አብራሪዎቹን ከመነሻው ሳይሆን እንደ አባይ እግረ መንገዱን ከሱዳን አሳፍሮ ነው የሚሄደው ማለት ነው፡፡
የጉድ ሃገር ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ!

ይህ ፓይለት ቦይንግ 767ን ከሚያህል ጠያራ ላይ በገመድ ከወረደ፤ ምናልባትም ቀደም ሲል ለአየር ሀይል ጀት አብራሪነት ተመልምሎ ወደ አየር መንገድ በመዛወሩ ከፍቶት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም፡፡

ረዳቱ አብራሪ አውሮፕላኑን ጠልፎና አስገድድ ጀኔቭ ያሳረፈው መሳሪያ ይዞና ዋናውን አብራሪ አስገድዶ ሳይሆን ዋናው አብራሪ ሸንት ቤት ቤት ሲሄድ ጠብቆ የአብራሪዎቹን ክፍል ከውስጥ በመቆለፍ ነው አሉ፡፡

አሁንም ‹‹አሉ››ን አትርሱና ፤ ይህ እውነት ከሆነ አየር መንገዳችን ለዋና አብራሪዎች ‹ኢትዮፒያን› የሚል ፖፖ ቢጤ አቅርቦ ከማብረሪያ ክፍላቸው ለሽንት እንዳይወጡ ማድረግ ሊኖርበት ነው ማለት ነው፡፡

መቸም እንግዲህ ወጣቱ ረዳት ፓይለት ጥፋተኛነቱ ከተረጋገጠ የሚጠብቀው እስር ከባድ ነውና፤ ቅጣቱን ለማቅለል ሲል ‹‹ጥገኝነትን ከታሪካዊ ጠላታችን ከጥልያን ከመጠየቅ ይልቅ ከገለልተኛዋ ከጄኔቫ መጠየቁ ይሻላል ብዬ ነው›› ሊል ይችላል፡፡

በአለም ላይ የፈለገው ሀገር ያውም አውሮፕላን አብርሮ ሄዶና ከአውሮፕላን ወርዶ ጥገኝነት መጠየቅ የሚችል ፓይለት የራሱን አውሮፕላን ጠልፎ ‹‹ጥገኝነት ስጡኝ›› ማለቱ ግን አሁንም የሚዋጥ አይደለም፡፡

የሆነ ሆኖ፤ ረዳት አብራሪው የጠለፋ ድራማውን ሲከውን፤ ‹ኢትዮፕያን› የሚል ስም የተሸከመው ጠያራ ነዳጅ ጨርሶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በሰላም ማረፉም ትልቅ ነገር ነው፡፡

ወትሮስ እኛን የቸገረን የከፋውና ያኮረፈው ሁሉ ሲጠልፍና ሲጠላለፍ ‹ኢትዮጵያችን› ነዳጅ እየጨረሰች፣ ካቀደችው ሳይሆን ካቀዱላት ስፍራ ማረፏ አይደል?

No comments:

Post a Comment